እውን አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) በአካሉ ሁሉም ቦታ ነው ያለውን???
አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) በአካሉ ሁሉም ቦታ ነው ብለው ሚሞግቱ ሰዎች ሙግታቸው ፍፁም ሃሰት ነው። ለመሆኑም ድግሞ ከነቅል(ቁርአንና ሱና) ማስረጃ ይሰጣቸዋል።
1፦ ነቅል፡
ሰምዕ፡ ይህም ማለት በመስማት ከሚታወቁት መረጃዎች ማለት ነው። አላህ የበላይ መሆኑን ለራሱ አፅድቋል። እናንተ የምታመጡት ማስረጃ ደግሞ ለምትፈልጉት ነገር ፍፁም አመልካች አይደለም። ምክንያቱም አብሮነት (መዕያ) ግዴታ በአካልና በቦታ ተገኝቶ መሆንን ብቻ ፈፅሞ አያሲዝም። ወደ ዓረቦች ንግግር አትመለከትምን?እንዲህ የሚሉ አባባላቸውን፦
" አልቀመሩ ማዓና ወመሃሉሁ ፊ ሰማእ" "ጨረቃው ከኛ ጋር ነው። ቦታው ግን ሰማይ ላይ ነው"
==>አንድ ሰው ባለቤቴ ከኔ ጋር ነችይላል። እርሱ ግን ያለው ምስራቅ ነው። እርሷ ደግሞ ምእራብ። አዛዥ ወታደሮቹን እንዲህ ይላቸዋል ወደ ጦር ሜዳው ሂዱ እኔም ከናንተ ጋር ነኝ። እርሱ ይህንሲናገር ግን ማዘዣ ክፍል ውስጥ ሆኖ እነርሱ ደግሞ የጦር ሜዳው ላይ ሆነው ነው። ስለዚህ አብሮ መሆን ሲባል ግዴታ በአካልና በቦታ አንድላይ መሆንን ብቻ አያመለክትም። ሌላው ይህ አብሮ መሆን (መዕያ) እንደየ አገባቡ ሊወሰን የሚችልበት ሁኔታ አለ። አንዳንዴ ይህ ወተት ከውሃ ጋር ነው ልንል እንችላለን። በዚህ ጊዜ ይህ አብሮነት መደባለቅን ያሲዛል። አንዳንድ ሰው እቃዬ ከእኔ ጋር ነው ይላል። እርሱ ግን ከእቃው ተለይቶ ቤቱ ነው ያለው። እቃውን ተሸክሞት ከእርሱ ጋር አድርጎትም ከሆነ እቃዬ ክእኔ ጋር ነው ይላል። ስለዚህ ይህ ቃል አንድ ቢሆንም እንደየ አገባቡ ትርጉሙም ሚለያይብት ሁኔታ አለ። ስለዚህም እንላለን ፦ አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) ከፉጡሮቹ ጋር የመሆኑ ሁኔታ ልክ እንደሌሎቹ ባህሪዎቹ ለርሱ በሚገባው መልኩ ነው። አዎ በማያሻማ መልኩ እርሱ ከፉጡሮቹ ጋር ነው። በአካሉ ደግሞ ከዓርሹ በላይ ነው።
(2) ፦ የአእምሮ ማስረጃ፡
ማለትም ይህ ሙግታቸው ሀሰት ለመሆኑ። እንላለን አላህ ከኔ ጋር ነው በሁሉም ቦታ ካልክ ይህ አባባል ፍፁም ሀሰተኛ ነገሮችን ያሲዛል።
1/ የቁጥር ብዛትን ወይም መከፋፈልን። ይህ ደግሞ ያለ ጥርጥር ውድቅ ነው።
2/ አንተ እርሱ በየቦታው ከእኔ ጋር ነው ካልክ ሰዎች በጨመሩ ቁጥር መጨመርንና በቀነሱ ቁጥር መቀነስን ያሲዛል።
3/ ሌላው የሚያሲዘው ነገር አላህን (ሱብሃነሁ ወተዓላ) ከቆሻሻ ቦታዎች ሳይቀር አለማጥራትን ነው። ምክንያቱም መፀዳጃ ቤትም ሆነህ አላህ ከእኔ ጋር ነው ካልክ ይህ እጅግ በጣም አላህን (ሱብሃነሁ ወተዓላ) ማጉደፍ ነው። የወሰድኩትከ" ዓቂደቱል ዋሲጥያ" ሸርህ ኢብን ዑሰይሚን። ፠፠ እዚህ ነጥብ ላይ እኔም ትንሽ ላክልበት እኛም በራሳችን አባባል እራሱ ጠዋት ላይ መስኮት ከፍተን ፀሃይዏ ገባች እንላለን። እርሧ ግን ያለችው ሰማይ ነው። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ፀሃይ ገባች በሚል ብንጠቀምም ለማለት የፈለግነው ግን " በአካሏ ሰማይ ብትሆንም ብርሃኗ ግን ቤታችን ገብቷል" ማለትን ነው። ለዚህም ትርጔሜ ተቃዋሚ አካል ፍፁም አይታወቅም። ምን አልባት ዛሬ ዛሬ አህባሽና መሰሎቻቸው ካልሆኑ በስተቀር። አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) ሁላችንንም ለጠቃሚ እውቀትና ለመልካም ተግባር ያድለን። አሚን
No comments:
Post a Comment