Wednesday, 12 March 2014

የሚያጓጓው ሰላም

አሰላሙ   ዐለይኩም ወረሕመቱላሂ ወበረካቱሁ
        ሰላም ሰላሙን ለተከተሉ ሁሉ ይሁን፡፡ እኛ ሙስሊሞች ሰላማዊ ነን ከሰላሙ ጌታ ሰላምን የምንመኝ፡፡ ስማችንም ሀይማኖታችንም ከሰላም ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እርስበርስ ስንገናኝ ከማንኛው የቃላት ልውውጥ በፊት ከየትኛውም ህዝብ በተለየ በቋንቋ የማይግባቡ ህዝቦችን የሚያግባባ ውብ፣ ድንቅ፣ አጭር አለማቀፋዊ ቋንቋ አለን- “አሰላሙ ዐለይኩም”(ሰላም በናንተ ላይ ይሁን)፣ “ወዐለይኩም አሰላም” (ሰላም በናንተም ላይ ይሁን)፡፡ እኛ እንደነጀምስ “ሀይ” እንደነ እንትና “ታዲያስ” … ብለን በጥያቄ፣ በነገር፣ በፉገራ፣ በመአት … አንጀምርም፡፡ ይልቁንስ በዱዐ ነው የምንጀምረው በመልካም ምኞት! ፊትን ፈታ አድርጎ፣ እዝነትና ትህትና በተላበሰ መልኩ “አሰላሙ ዐለይኩም!”
ኢስላም፣ ኢስቲስላም፣ ሙስሊም፣ ሰላም፣ …!! ከጌታችን ስሞች አንዱ አሰላም ነው፡፡ ከአምስቱ እለታዊ ግዴታዎቻችን ከሶላቶቻችን በኋላ ከአሰላሙ ከጌታችን ሰላምን እንለምናለን፣
“አላሁመ አንተስሰላም፣ ወሚንከስሰላም፣ ተባረክተ ያዘልጀላሊ ወልኢክራም” በማለት “ጌታችን ሆይ! አንተ ነህ ሰላሙ፤ ሰላምም ካንተ ነው፤ በስምህ የሚገኘው በረከት ሰፋ፤ አንተ የልቅናና የቸርነት ባለቤት ሆይ”፡፡

ብንገናኝ፣ ብንለያይ፣ ብንፀልይ፣ ብንወያይ፣… በሰላም ነው፣ ለሰላም፣ ስለሰላም! ጌታችን አሰላም፣ የምንመኘው አገር ዳሩስሰላም፣ የሰላሙ ሀገር-(ጀናህ)! የሰለላሙም አገር ሰላምታ ሰላም ነው፣ “ወተሒየቱሁም ፊሃ ሰላም፡፡” ከአንድየው ከአሰላሙ የሚመጣውም ብስራት ሰላም ነው፣ “ሰላሙን ቀውለን ሚን ረቢን ረሒም፡፡” “ለጀነትም ነዋሪዎች አዛኝ ከሆነው ጌታ በቃል ሰላምታ አላቸው” በሰላሙ ሀገር በጀናህ የሚሰማውም ወሬ ረብ- የለሽ እና እንቶ ፈንቶ ሳይሆን ሰላም ነው፣ “ኢላ ቂለን ሰላመን ሰላማ፡፡” ሱብሐነላህ! አሁን እንደ ኢስላም ለሰላም ትልቁም ዋጋ የሰጠ አለ?! ሙስሊም መሆን ምን አይነት እድል ነው? ውስጣዊ ሰላምን የሚያጎናፅፍ ልዩ ተድላ?! ሙስሊም ነዎት?! አላሁ አክበር!! የታላቅ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል! ያሸነፉት ሎተሪ አይደለም! በጭራሽ! ያሸነፉት ለሰው-በላ ጭራቆች፣ ለፀረ-ሰላም ሀይሎች ለነሻሮን ወንድሞች ጭምር የሚሰጠውን የነጀምስን የኖቤል የሰላም ሽልማትም አይደለም፡፡ ሽልማትዎ አይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ በሰው ልቦና ውስጥ ፍፁም “ውል” ብሎ የማይወቅ እጅግ ውድና አጓጊ ነገር ነው! ሽልማትዎ ይሄውና! ከባለሰላሙ ጌታ ከአሰላሙ በኢማን ለታጀበው የሰላም ትጋትዎ ዳሩስሰላም! ጀናህ!! “ፈመንዙህዚሀ ዐኒናሪ ወኡድኺለል ጀነተ ፈቀድ ፋዝ!!!” ከዚህ የሚበልጥ ምን ሽልማት አለ? አያሽቀዳድምም? “ወሳሪዑ ኢላመግፊረቲን ሚን ረቢኩም ወጀነቲን ዐርዱሀስሰማዋቱ ወልአርዱ ኡዒደት ሊልሙተቂን!”
ሙስሊም ሙስሊማት ዒባዱስሰላም! የአዛኙ የአሰላም ባሪያዎች በምድር ላይ ሲጓዙ በሰኪና ነው በትህትና በሰላማዊ ሁኔታ፡፡ ቂሎች፣ ከቂል የሚጠበቁ ቃላትን ቢወረውሩባቸው፣ በቂልኛ ቢያናግሯቸው፣ ፀረ-ሰላም ሚሳኢል ቢያስወነጭፉባቸው፤ ኢላማውን በማይስተው የሰላም ሚሳኢል ያከሽፉታል፣ አቅጣጫ ያስቀይሩታል፡፡ “ሰላም” በማለት፣ ሰላም በመመለስ፣ በሰላምኛ በማናገር፡፡ የኢማን፣ የኢስላም፣ የሰላም አርአያዎቻችን ከአሰላሙ ጌታችን ለተቀበሉት የሰላም አደራ- ለኢስላም ሲሉ የደሙት፣ የቆሰሉት፣ የተሰቃዩት፣ የሞቱት ነቢዮቻችን ናቸው፡፡ እነዚያ በአስፈሪው የቂያማህ ጭንቅ ጊዜ እንኳ ስለ ሰላም ዱዐ የሚያደርጉት “አላሁመ ሰሊም ሰሊም” በማለት፡፡ ሰላም በነሱ ላይ ይሁን፡፡
ውድ የኢስላም አጋሮቼ! እንቁ የኢስላም ወገኖቼ! በኢስላም ከአስሰላም ዳሩስሰላምን እንፈልግ፡፡ በኢስላማዊ ሰላምታችን ደግሞ ሰላማዊ ህይወት ለመጎናፀፍ የሚያግዘንን “አጅር” እንሰብስብ፡፡ ሰላምታን እናብዛ፡፡ የሰላም ሀዋሪያው ሰላም ወዳዱ ዐብዱላህ ኢብኑ ሰላም ረዲየላሁ ዐንሁ ከሰላሙ አርበኛ ከውዱ ነቢያችን ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲላህ ዐለይሂስሰላም እንዲህ የሚል የሰላም መልእክት አስተላልፏል፡- “እናንተ ሰዎች ሆይ! ሰላምታን አብዙ፣ የተራበን አብሉ፣ ዝምድናን ቀጥሉ፣ ሰዎች ሲተኙ በሌሊት ስገዱ፣ ጀነትን በሰላም ትገባላችሁ፡፡” ሱብሑነላህ! እስኪ እነኚህን ውብ ቃላት እናጣጥማቸው! ቃላቱ፣ ስኬቱ፣ መልእክቱ፣ ሰአቱ፣ ሂደቱ፣ ውጤቱ፣ ሁሉ ሰላም!! የነኚህን ቃላት ዐረብኛ ወዝ ላጣጣመ ደግሞ ሌላ እርካታ፣ ሌላ ጣዕም፣ ሌላ ሰላም!!
                                                                  ውድ ሙስሊሞች የሰላም ሀይሎች የዳሩስሰላም ናፋቂዎች ከአስሰላም፣ ከአርረሕማን የተጣለብንን ሀላፊነት እንወጣ፣ ሰላማችንን እንዳናጣ፡፡ “አሰላሙ ዐለይኩም” እንባባል፡፡ የተሻለውን ጥለን የወራረዱ አንለቃቅም፡፡ ሰላምታችን ኮተት የለውም አያሳፍርም፡፡ ሰላምታችን ቦምብ አይደለም አያስፈራም፡፡ ሰላም እንዴት ያስፈራል?
                       ወሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ፡፡         
ኢብኑ ሙነወር

No comments:

Post a Comment