Wednesday, 12 March 2014

ተውሂዱል አስማኢ ወሲፋት

ተውሂዱል አስማኢ ወሲፋት
ተውሂዱል አስማኢ ወሲፋት ማለት፤ “አላህን በስሞቹና በባህሪዎቹ አንድ ማድረግ” ሲሆን፤ በቁርዓንና በሐዲስ የተረጋገጡትን የአላህን ያማሩ ስሞችና የላቁ ባህሪዎች ተቀብሎ ማጽደቅ፣ በውስጣቸው ያዘሉትን ትክክለኛ መልዕክት ለአላህ ማረጋገጥ እንደዚሁ አላህ እና መልዕክተኛው ዉድቅ ያደረጓቸዉን ባህሪዎች ውድቅ ማድረግ፤አላህ በስሞቹና በባህሪዎቹ ምንም አምሳያና አጋር የሌለው ብቸኛ አምላክ መሆኑን ማመንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
አስፈላጊነቱ እና በኢስላም ውስጥ ያለው ታላቅ ቦታ
 የአላህን ስሞችና ባህሪዎችን በተመለከተ መረጃዎችን በማጥናትና በማወቅ ትክክለኛውን መስመር መከተል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ጥናቱን ከመጀመሩ በፊት ይህ የተውሂድ ዘርፍ በኢስላም ውስጥ ያለዉን ታላቅ ቦታ እና አሳሳቢነቱን ማወቁ እጅግ ይረዳዋል። ስለሆነም አስፈላጊነቱን እና በኢስላም ውስጥ ያለውን ታላቅ ቦታ በተከታዮቹ ነጥቦች ለመጠቆም እንሞክራለን።
 1- ከዕውቀት ዘርፎች ሁሉ የበለጠና ክብር ያለው የአላህን ስሞችና ባህሪዎች የሚያሳውቀው ይህ የተውሂድ ዘርፍ ነው። የማንኛውም እውቀት ክብር የሚለካው እርሱን በመጠቀም የሚታወቀው ነገር ባለው ታላቅነት ነው። ከአላህ በበለጠ ታላቅ የሆነ እና ክብር የሚገባው የለም። ስለዚህ የአላህን ስሞችና ባህሪዎች የሚያሳውቀው የትምህርት ዘርፍ ከእውቀቶች ሁሉ የላቀ እና ክብር ያለው እውቀት ነው።                                                          2- የአላህን ስሞችና ባህሪዎች ማወቅ አላህ ፍጡራንን ከፈጠረባቸው አላማዎች ውስጥ አንዱ ነው። ለሌላ እውቀት መንደርደርያ ሳይሆን በእርሱነቱ የሚፈለግ ነው። አላህ ሰማያትን እና ምድርን የፈጠረው ሁሉን አዋቂ እና በሁሉም ነገር ላይ ቻይ እንደሆነ ባሮች ያውቁ ዘንድ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፦
«አላህ ያ ሰባትን ሰማያት ከምድርም መሰላቸውን የፈጠረ ነው፡፡ በመካከላቸው ትእዛዙ ይወርዳል፡፡አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ መኾኑን አላህም ነገሩን ሁሉ በዕውቀት ያካበበ መኾኑን ታወቁ ዘንድ ነው» (ጠላቅ 12)
 3- በሰለፎችና በቢድዓ አራማጆች መካከል ብዙ የክርክር መድረኮችን ያስከፈተውና ብዙ ውዝግብ የበዛበት ርዕስ በመሆኑ ትኩረትን ይሻል። ይህ አጀንዳ ብዙ የቢድዓ አራማጆች ማደናገርያ ብዝታዎችን የፈበረኩበት በመሆኑ ማንኛውም ሙስሊም በቁርዓን እና በሱና በተረጋገጠው መልኩ ጠለቅ ያለ እውቀት ሊኖረው ይገባል። ከብዥታዎችና ማምታቻዎች መጠበቅ የሚቻለው በእውቀት ብቻ ስለሆነ ውዝግቦችን ሁሉ በአላህና በመልዕክተኛው ንግግሮች ለመዳኘት ብዥታዎችንም ለማስወገድ የዚህ ዘርፍ እውቀት ያስፈልጋል።                                       4- አላህን በሚገባ ያወቀ ሰው እርሱን በጣም ይፈራል። አላህን በባህሪዎቹ ያወቀው ሰው ልቡ በብርሀን ይሞላል። በልቡ የሚሰፍረው የአላህ ውዴታ ከአመጽ ሁሉ ይጠብቀዋል። አላህን በመታዘዝ እና ዘወትር በማምለክ የተዋበ ጣፋጭ ህይወትን ይኖራል።                                                                              5- የዚህ ኡማህ ቀደምት ትውልድ የሆኑት ሰለፎች ዘንድ የነበረሩ እውቀቶች በጥቅሉ ሲታዩ፤ አላህን ማወቅ እና ለአላህ መስራት ነበሩ። ይህ እውቀታቸው በጠንካራ መረጃዎች ላይ የተገነባ ነበርና ያወቁትን እንዲተገብሩ ይገፋፋቸው ነበር። የእውቀታቸው ግማሽ አላህን ማወቅ ነበር። ስለዚህም፤ የተውሂዱል አስማኢ ወሲፋት የዕውቀት ዘርፍ በሰለፎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ነበረው።                                                                                                 6- የአላህን ስሞችና ባህሪዎች ማወቅ ያሉት መልካም ውጤቶችና ፍሬዎች እጅግ ብዙ ናቸው። እያንዳንዱን የአላህ ስም እና ባህሪ ማወቅ እራሱን የቻለ አምልኮ ነው። ለምሳሌ፤                                        አላህ ሰሚ፣ ተመልካች እና ሁሉን አዋቂ መሆኑን ያመነ ሰው አንደበቱን እና አካሉን አላህ ከማይወደው ነገር እንዲጠብቅ ያደርገዋል። አንድ የአላህ ባርያ የአላህን ስሞች እና ባህሪዎች ባወቀና ባመነባቸው ቁጥር ወደ አላህ እየቀረበ ይሄዳል። ሁሉንም የዒባዳ አይነቶች ብናስተውል የአላህ ስሞችና ባህሪዎች ግዴታ የሚያደርጓቸው ናቸው።
ያለ “ተክይፍ” እና ያለ “ተምሢል” ومن غير تَكْييفٍ وَلا تَمْثِيل

አህሉሱና የአላህን ባህርያት ሲያፀድቁ ከማመሳሰልና የባህሪውን ሁኔታ ከመናገር ይርቃሉ። ይህ ደግሞ የአህሉሱናን ዓቂዳ የአላህን ባህሪዎች ከፍጡራን ባህሪዎች ጋር ከሚያመሳስሉት ሙሸቢሀዎች (ሙመሲላዎች) አቂዳ ይለያል። 

No comments:

Post a Comment