***«ለዱዓ መሰባሰብ»***
ይህ ብሂል ከመልዕክተኛው ተወዳጅ አጎት ዐብ-ባስ ኢብኑ ዐብዲ’ል-ሙጥ-ጠሊብ የተላለፈበት ዘገባ ደካማ ቢሆንም የተለያዩ የቁርኣንና የሐዲሥ አስረጆች የሚደግፉት የጥበብ ቃል ነው!
እናም የተጋረጠውን መዓት አላህ እንዲያነሳልን በዱዓ፣ በንሰሃና በሰናይ ተግባራት ፊትን ወደ እርሱ ማዞር የግድ ይላል። መልዕተኛው (ﷺ) እንዲህ ማለታቸው ይወራል፦
صدقةُ السّر تطفئ
غضبَ الرب، وصنائعُ المعروف تقي مصارعَ السوء..
«የሚስጥር ሰደቃ የጌታን ቁጣ ታጠፋለች፤ በጎ ውለታዎችም ከመጥፎ ውድቀት ይጠብቃሉ..» [“ሲልሲለቱ’ል-አሓዲሥ አስ-ሶሒሓህ” ቁጥር 1908]
ሆኖም ይህንን በማቀድ አንድን የአምልኮ ተግባር በህብረት ለመፈፀም ጊዜ ወስኖ በቀጠሮ መሰባሰብ የተደነገገው ዝናብን ለመለመን በሚከናወነው የ“ኢስቲስቃእ” ሰላት ላይ ብቻ እንደሆነ አንዳንድ ሊቃውንት ይጠቁማሉ። ለምሳሌ፦
- አል-ሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር በዘመናቸው በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ሰው የሚሞትበት ወረርሽኝ በአገራቸው (ግብፅ) ተከስቶ እያለ አንዳንዶች ለዱዓ በአንድ ሜዳ መሰባሰብን ቢፈቅዱም እርሳቸው ግን ይህ የተደነገገ ቢሆን ኖሮ በቀድምት ትውልዶችና ሊቃውንት ላይ የሚሸሸግ እንዳልነበር በመጥቀስ ቢድዓህ እንደሆነ አስረድተዋል ። [“በዝሉ’ል-ማዑን” ገፅ 328-330]
- እንዲሁም አስ-ሱዩጢ ስለጉዳዩ እንዲህ ይላሉ፦
«ተቆጥረው የማይዘለቁ ሰሓቦችና ታቢዒዮች የነበሩበት የመጀመሪያው ትውልድ በተደጋጋሚ የወረርሽኝ ችግር ላይ ወድቆ ነበር፤ እነርሱም የህዝበ-ሙስሊሙ ሁሉ ምርጦቹ ናቸው! ሆኖም አንዳቸውም ይህንን አላደረጉም፤ እንዲደረግም አላዘዙም! ምርጥ ታቢዒዮችና ተከታዮቻቸው በነበሩበት ሁለተኛው ክፍለ-ዘመንም እንደዚሁ! በሶስተኛውና በአራተኛው ክፍለ-ዘመንም እንደዚሁ!..» [“ማ ረዋሁ’ል-ዋዑን ..” ገፅ 168]
- ኢብኑ ዓቢዲን የተባሉት ታዋቂው የሐነፊይ-ያህ ምሁርም የኢብኑ ሐጀርን መልስ ካመላከቱ በኋላ እንዲህ ይላሉ፦
ولو قيل بتحريمه لكان
ظاهرا؛ لأنه إحداثُ كيفيةٍ يَظنّ الجهّالُ أنها سنّة
«ጭራሽ “እርም (ሐራም) ነው!” ቢባል (ከመረጃ አንፃር) የጎላ ይሆን ነበር፤ ምክንያቱም ይህ መሃይማን እንደ ሱን-ናህ ሊቆጥሩት የሚችል አዲስ አፈፃፀም መፍጠር ነውና!»
[“ኑዝሀቱ’ን-ነዋዚር” (455)]
እንዲያውም ከዚህ ውጭ ባለው ሁኔታ እንኳ መሰባሰብ ከተደነገገባቸው ተግባራት ውጭ እንደ ዱዓ ያሉ የአምልኮ ስርዓቶችን በህብረት ለመፈፀም መጠራራትን ብዙ የኢስላም ሊቃውንት አይደግፉም።
- ለምሳሌ፦ አል-ኢማም አሕመድ እንዲህ ተብለው ተጠየቁ፦ “ሰዎች ተሰባስበው አላህን መለመናቸውና እጃቸውንም ማንሳታቸው ይጠላል?”
እሳቸውም፦
مَا أَكْرَهُهُ
لِلْإِخْوَانِ إذَا لَمْ يَجْتَمِعُوا عَلَى عَمْدٍ إلَّا أَنْ يَكْثُرُوا.
= «ካልበዙ በስተቀር ሆን ብለው ካልተሰባሰቡ ለ(ዲን) ወንድማማቾች አልጠላውም!»
አል-ኢማም ኢስሓቅ ኢብኑ ራሃወይህ ሲጠየቁም ተመሳሳይ መልስ ሰጥተዋል።
«ካልበዙ በስተቀር» ሲሉ ልማድ በማድረግ እስካልተበራከቱ ድረስ ማለታቸው እንደሆነ ጠያቂው (ኢስሓቅ ኢብኑ መንሱር) ተናግረዋል!
[“መሳኢሉ’ል-ኢማሚ አሕመድ ወኢስሓቅ” (9/4879)፣ “አል-ኣዳብ አሽ-ሸርዒይ-ያህ” ሊ’ብኒ ሙፍሊሕ (2/103)]
አላህ ይበልጥ አዋቂ ነው።
በሸይኸ ኢሊያስ አህመድ
No comments:
Post a Comment