Wednesday, 2 April 2014

በጥሩ ማዘዝ እና ከመጥፎ መከልከል

               በጥሩ ማዘዝ እና ከመጥፎ መከልከል 

              አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ እንዲህ ብሏል።
“ለሰዎች ከተገለፀች ህዝብ ሁሉ በላጭ ሆናችሁ። በጥሩ ታዛላችሁ ከመጥፎም ነገር ትከለክላላችሁ በአላህም(አንድነት ) ታምናላችሁ።”  (አል-ዒምራን፡110) 

ከኑዕማን እብኑ በሺር (ረድየላሁ ዓንሁ) እንደተወራው የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፦

“የአላህ ድንበር ላይ ቀጥ ያለ ሰው ከሚጥሰው ጋር ያለው ምሳሌ መርከብ ላይ እጣ እንደተጣጣሉት ሰዎች አይነት ነው ምሳሌው ። ገሚሱ ከላይ ሲሆን ገሚሱ ደግሞ ከታች ሆነ። ታዲያ ከታች የነበሩት ውሃ ሲጠማቸው በላኞቹ ላይ ያልፋሉ። አሉም እኛ ለራሳችን የሆነን ቀዳዳ ብናዘጋጅ ከበላያችን ያሉትን አናስቸግርም። (እነዚህ ሰዎች) በፈለጉት ነገር ከተተው ሁሉም ይጠፋሉ። እጃቸውን ከያዟቸው ግን እነርሱም ሁሉም ነፃ ይወታሉ።” (ቡኻሪ ዘግበውታል)

ከአንቀፁ  የሚወሰዱ ቁም ነገሮች
1) በጥሩ ማዘዝና ከመጥፎ  መከልከል ሙስሊሞች ከሌሎች ከሚለዩበት መሰረቶች አንዱ ነው። 
2) ይህን ካልፈፀሙ ደግሞ የበታቾች ይሆናሉ። ምክንያቱም በርሱ በላጭነት ስለተረጋገጠላቸው እርሱን ከተው ደግሞ ተበላጭ ሆነው የበታችነት ይረጋገጥባቸዋል።
ከሃዲሱ ሚወሰዱ ቁም ነገሮች
1) በጥሩ ማዘዝና ከመጥፎ መከልከል አንድ ሰው እራሱንም ሆነ ሌሎቹን ነፃ ሚያወጣበት መሰረት ነው።
2) መጥፎ ስራን አሊያ መጥፎ ሰሪን አለመከልከል ለሰሪውም ለሌሎችም መጥፊያ ሰበብ ነው።
      አዎ መርከቢቷን ከታች ለመቅደድ ያለሙትን ቂሎች አዋቂዎች መከልከል ካልቻሉ ነፍስ አድን እንኳ ሊያተርፋቸው በማይችል መልኩ ሁሉም ተያይዘው ይሰጥማሉ። ምሳሌ፦  
አንድ ሰው ቤት ሲቃጠል ቢመለከት ነጭ ጥቁር ዘመድ ባዳ ወዘተ ሳይል እንዲያውም ከራሱ አልፎ  ሌሎችን በመጥራት እሳቱን ለማጥፋትና በውስጡ ያሉትን ለመታደግ ይረባረባል። ምክንያቱም፦
አንደኛ ሰውንም ይሁን  ንብረትን ከዚህ ሰቆቃ ለማዳን ሲሆን ሌላው ደግሞ  በዋዛ ፈዛዛ ወደራሱ መቶ ጭማሪ ሰለባ እንዳይሆን በመስጋት ነው። 
      ታዲያ አንተ በጥሩ ማዘዝን እና ከመጥፎ መከልከልን ተቃዋሚ ሆይ፡  ወንድምህ ከዚህ የዱንያ እሳት የበለጠ ለሆነው የ "ጀሃነም " ረመጥ አንዲ በ "ቢድዓ" አንዴ በ"ወንጀል" እራሱን ሲያዘጋጅ አለፍም ሲል በ"ሽርክ " እየዋዠቀ በውስጡ ለመዘውተር እራሱን ሲያጭ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለትህ ለምንድነው ??? ይህ በእውነቱ ጠላትነት እንጂ ወዳጅነት ነውን ??? መልሱን ለአዋቂዎች።
አንተ የሆነ ግብዣ ለይ ዘንጠህ በተለይ እንደነጭና መሰል አትንኩኝ ባዮች አልባሳትን ለብሰህ ልትሄድ በተሰየምክበት ሰአት ወንድም ቆሻሻን አይቶብህ አሽሟጦ ቢሸኝህ ከዚህም ይባስ ሲል የእድምተኞቹ መጠቋቆሚያ ሆነህ በእፍረት ካባ ብትመለስ =ያ ወንድም = ያንተን ውድቀት ገላጊ ፡ ውበትና ድምቀትህ ሰላም የሚነሳው ጠላትህ ለመሆኑ ከዚህ ያለፈ ማረጋገጫን ባልፈለክለት ነበር። 
     ታዲያ ለምንድነው እህት ወንድሞችህ ነገ ልእሉ ፈጣሪያቸው ፊት በሽርክ በቢድዓ በወንጀል መከራ ጠቁረውና ጎድፈው ለመቅረብ ሰቃረቡና ሲበቁ ያለ ቅንጣት ርህራሄ ጀርባህን የሰጠሃቸው ? መልሱን ለአስተዋዮች።
በዚሁ አጋጣሚ ፍፁም ሳይጠቀስ የማይታለፈው አንገብጋቢ ጉዳይ ቢኖር ይህን ብርቅዬ የእስላም መሰረት ከስር መሰረቱ ገንድሰው የጣሉት የ " ኢኸዋነል ሙስሊሚን " አካሄድ ነው። እነርሱ እራሳቸውንም ይሁን ሌሎችን ለመመልመል ያስቀመጡት ትልቅ ህገ ደንብ (ቃዒዳ) አላቸው። እርሱም እንዲህ የሚል ነው። " በተስማማንበት ነገር ላይ እንሰባሰባለን። ባልተስማማንበት ነገር ደግሞ ከፊሉ ለከፊሉ ምክንያትን ያቀርባል።" 
አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ )  እንዲህ ይላል።
 "በበጎ ነገርና አላህን በመፍራት ተረዳዱ። ግን በሃጢአትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ።"                 (ምእራፍ አል ማኢዳህ አንቀፅ 2)
እዚህ ጋር እንግዲህ በበጎ  ነገር ከሆነ አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) እንዳለን ተስማምተንና ተባብረን እንጓዛለን። የዚህ ተቃራኒ በመጥፎ ነገሮች ማለትም በሽርክ ፡ በቢድዓ ፡ በወንጀል ከሆነ አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ ) እንዳለን አንዱ ሌላውን መከልከልና በዚህም ላይ አለመተባበር ነው ወይስ "እኸዋኖች" እንደሚሉት ምክንያት(ዑዝር) እየተሰጣጡ በሃሰት አንድነት መተሻሸት ??? መልሱን ለፍትሃዊዎች። 

          በእውነቱ ያ ከእርሱ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ በሌለው አላህ ይሁንብኝ በጥሩ ማዘዝንና ከመጥፎ  መከልከልን " ነቅል " አይደለም " አቅል " ም የሚያረጋግጠውና ግዴታ የሚያደርገው ታላቁ የኢስላም መሰረት ነው። አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ ) ሁላችንንም ጠቃሚ እውቀትንና መልካም ተግባርን ያድለን። አሚን


by Ummu Abdellah Muhammed on Sunday, December 21, 2012 at 10:11am 

No comments:

Post a Comment