Wednesday, 27 January 2016

የነብያት ሁሉ ጥሪ!

የነብያት ሁሉ ጥሪ!
አላህ በተለየዩ ዘመናት በርካታ ነቢያትን ልኳል፡፡ እነዚህ ነብያት ለተላኩላቸው ሕዝቦች ያስተምሩ የነበረው የአላህን ብቸኛ አምላክነት የሚገልፀውን (ተውሂድ አል ኡሉሂያ) የተውሂድ ክፍል እንደነበረ ቅዱስ ቁርአን ይነግረናል፡፡
وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولًا أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ وَاجْتَنِبُوا الطَّاغُوتَ ۖ فَمِنْهُم مَّنْ هَدَى اللَّهُ وَمِنْهُم مَّنْ حَقَّتْ عَلَيْهِ الضَّلَالَةُ ۚ فَسِيرُوا فِي الْأَرْضِ فَانظُرُوا كَيْفَ كَانَ عَاقِبَةُ الْمُكَذِّبِينَ [١٦:٣٦]
‹‹በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፡፡›› (አል ነህል 36) 
በሱረቱል አንቢያ ውስጥም አላህ (ሱ.ወ)  ወደየህዝቦቻቸው ስለላካቸው መልዕክተኞች ለነቢያችን ሲገልፅላቸው እንዲህ ይላል፡
وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ [٢١:٢٥]
‹‹ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡›› (አል አንቢያ 25)
  በየዘመናቱ ወደ ሕዝቦቻቸው የተላኩ ነቢያት በአቂዳ ዙሪያ ጠንከር ያለ የፀና አቋምና እምነት እንዲኖራቸው ነበር፡፡ ሕዝባቸውን ያስተምሩና ይመክሩ፣ ያስጠነቅቁና ይዘክሩ የነበረው፡፡ አብዛኛው ህዝብ  ግን ጌታቸው ለእርሱ የዋለውን ውለታና የሰጣቸውን ውለታ አስተባበሉ፡፡ በአመፀኛነታቸውም ገፉበት፡፡
  በአቂዳ ዙሪያ ባሉ የዲን ጉዳዮች ማወላወል ፈፅሞ የለም፡፡ የሐቀኛ ምዕመናን የአህሉ ሱና ወልጀመዓ የሕይወት መመሪያ የሆነውን ቁርአንንና የነብዩን () ሱና ሙሉ በሙሉ መከተል ብቻ ነው፡፡ በየዘመናቱ የላኩት ነቢያትም ያስተማሩት ይህንኑ ነው፡፡
ነብዩላሂ ኢብራሂም
  በአላህ አንድነትና እሱን ብቻ ስለመገዛት ባለው የተውሂድ አስተምህሮ ነብዩላሂ ኢብራሂም  የሕይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል የመጨረሻ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ የስጋ ዘመዶቻቸውና የገዛ ቤተሰባቸውን ጨምሮ ህዝባቸው በጠላተነት ተነስቶባቸዋል፡፡ የአላህ መልዕክተኛ ነበሩና በማያልቅበት ቸርነት፣ በአስደናቂው ተአምራቱ፣ በመለኮታዊ የበላይነቱ ጥበቃው አልተለያቸውም፡፡
      ለአላህ ሲታዘዙ ቅንጣት የማያወላውሉ በመሆናቸውም የአላህን የወዳጅነት ማዕረግ ለመጐናፀፍ በቅተዋል፡፡ ተውሃድን በተመለከተ ታላቁ ሞዴል አርአያ ነብዩላሂ ኢብራሂም ናቸው፡፡ ይህንንም በተመለከተ አላህ እንዲህ ገልፆልናል፡-
قَدْ كَانَتْ لَكُمْ أُسْوَةٌ حَسَنَةٌ فِي إِبْرَاهِيمَ وَالَّذِينَ مَعَهُ إِذْ قَالُوا لِقَوْمِهِمْ إِنَّا بُرَآءُ مِنكُمْ وَمِمَّا تَعْبُدُونَ مِن دُونِ اللَّهِ كَفَرْنَا بِكُمْ وَبَدَا بَيْنَنَا وَبَيْنَكُمُ الْعَدَاوَةُ وَالْبَغْضَاءُ أَبَدًا حَتَّىٰ تُؤْمِنُوا بِاللَّهِ وَحْدَهُ       [٦٠:٤]
‹‹በኢብራሂምና በእነዚያ ከእርሱ ጋር በነበሩት (ምእምናን) መልካም መከተል አለቻችሁ፡፡ ለሕዝቦቻቸው «እኛ ከእናንተ ከአላህ ሌላ ከምትግገዙትም ንጹሖች ነን፡፡ በእናንተ ካድን፡፡ በአላህ አንድ ብቻ ሲኾን እስከምታምኑ ድረስ በእኛና በእናንተ መካከል ጠብና ጥላቻ ዘወትር ተገለጸ፡፡» ባሉ ጊዜ (መልካም መከተል አለቻችሁ)፡፡›› (አል ሙምተሂናህ 4)
ነብዩላሂ ኢብራሂም ከህዝቦቻቸው ጋር ከፍተኛ ክርክር ስላደረጉበት ነው ይህ የቁርዓን አንቀፅ የሚያስረዳው፡፡ ይህን ክርክራቸውንና የውይይታቸውን ውጠት አላህ በሱረቱል አንቢያ 51-57 ባሉ አንቀፆች አብራርቶቃል፡፡ ይህንንም አጠር አድርገን ስንመለከተው፡-
 ነብዩላሂ ኢብራሂም  ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ወገኖቻቸው ከእንጨትና ከድንጋይ ከወርቅና ከመሰል ግዑዞች የተሰሩ ልዩ ልዩ ቅርፃ ቅርፆችን ያመልኩ ነበር፡፡ ነብዩ ኢብራሂም ይህ የወገኖቻቸው ድርጊት አላህን ከመገዛት እውነተኛ ጐዳና ያፈነገጠ መሆኑን በመገንዘባቸውም፡-
إِذْ قَالَ لِأَبِيهِ وَقَوْمِهِ مَا هَٰذِهِ التَّمَاثِيلُ الَّتِي أَنتُمْ لَهَا عَاكِفُونَ [٢١:٥٢]
‹‹ይህቺ ቅርፃ ቅርፅ ይህቺ እናንተ ለእርሷ (ዘውትር) አምላኪዎች የሆናችሁት ምንድናት?›› (አል አንቢያ 52)
በማለት የወገኖቻቸውን ከንቱ የባዕድ አምልኮ በማናናቅ ጠይቀዋቸዋል፡፡ እነሱም
‹‹አባቶቻችን ያመልኩ ነበር፣ እኛም የእነርሱን መንገድ ተከትለን እናመልካለን››
በማለት መልሱላቸው፡፡
ጣዖታትን ማምለክ ስህተት መሆኑን በመግለፅ ሊመለክ የሚገባው አንድ አላህ ብቻ መሆኑን በድፍረት አስተማሩ፡፡ እኒህ ጣዖታት ከቶም አንዳች ጥቅም እንደሌላቸው፣ ራሳቸውን እንኳ መከላከል እንደማይችሉ፣ በማንም ላይ ጉዳት የማድረስ አቅምና ችሎታ የሌላቸው፣ ጥቃት ቢደርስባቸው እገሌ ነው ብለው መናገር ወይም መጠቆም የማይችሉ አቅመቢስ መሆናቸውን በመግለፅ እይተነተኑ አስተማሩ፡፡
ህዝቡ ከጥመቱ የተነሳ ለተደረገለት የቅን መንገድ ጥሪ ዳዕዋ የሰጠው ምላሽ በእጅጉ የከፋ ነበር፡፡
قَالُوا حَرِّقُوهُ وَانصُرُوا آلِهَتَكُمْ إِن كُنتُمْ فَاعِلِينَ [٢١:٦٨]
«ሠሪዎች እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት፡፡ አማልክቶቻችሁንም እርዱ» አሉ፡፡ (በእሳት ላይ ጣሉትም)፡፡›› (አል አንቢያ 68)
እጅግ ከባድ የሆነ እሳት አቀጣጠሉና እዚያ ውስጥ ጣሏቸው፡፡ አላህ ኢብራሂም አንዳች ችግር ሳይደርስባቸው በሰላምና በጤና ይወጡ ዘንድ ስለፈቀደ እንዲህ የሚል መልዕክት ለእሳቷ አስተላለፈ፡
قُلْنَا يَا نَارُ كُونِي بَرْدًا وَسَلَامًا عَلَىٰ إِبْرَاهِيمَ [٢١:٦٩]
«እሳት ሆይ! በኢብራሂም ላይ ቀዝቃዛ፤ ሰላምም ሁኚ» አልን፡፡ (አል አንቢያ 69)

No comments:

Post a Comment