ዓቂዳ በዐረብኛ ቋንቋ “አሰረ ፣ አጠበቀ ፣ ቋጠረ…” ከሚሉ ጥሬ ቃላት የተገኘ ነው፡፡ የስርወ ቃል ትርጉሙም በኃይል አጥብቆ መቋጠርን ያመለክታል፡፡ የአብዛኛዎቹ ኡለማዎች (ኢስጢላሀዊ) የስስምነት ፍቺ በአማኙ ዘንድ ፍፁም ጥርጣሬ የሌለበት ቁርጥ ያለ እምነት (ኢማን) ማለት ነው፡፡
ኢስላማዊ አቂዳ አላህን በጌትነቱ፣ በአምላክነት፣ በስሞቹና በባህሪያቱ ብቸኛ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ዋና ዋና የኢማን መሰረቶች በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጻህፍቱ፣ በመልዕክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በቀደር (ክፉም ሆነ ደጉ በአላህ ቅድመ ውሳኔ መሆኑን) ማመንን መሰረት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በተረጋገጠ መልኩ በተላለፉት የዲን መሰረቶችና መርሆዎች፣ ከህዋሳት ግንዛቤ በራቁ (የገይብ) ጉዳዮች ማመንን ይጨምራል፡፡
ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት ኢስላማዊ አቂዳ አላህ ለባሪዎቹ ለመረጠው፣ የወደደውና የሰጠው ብቸኛ እምነት መሆኑን ማወቅና በፍፁም ልብ መቀበል ይገባል፡፡ ይህም ሲባል በእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወርቃማ የእስልምና ክፍለ ዘመናት የኖሩት ሰሀባዎች እና ታዕቢዮች የተጓዙበትን ቅን የእምነት ጐዳና የተከተሉ የሐቀኛ ምህመናን የአሕሉ ሱና ወልጀመዓ እምነት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢስላማዊ አቂዳ ሌሎች እሱን የሚያመለክቱና የሚተኩት ተላዋጭ መጠሪያዎች አሉት፡፡ እነርሱም አተውሂድ፣ አሱንና፣ ኡስሉዲን፣ አልፊቁሀል አክበር፣ አሸሪዓ እና አል ኢማን በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡
ዓቂዳ የሰዎች ሁሉ መሰረት
የሰው ልጆች ሁሉ ሲፈጠሩና ወደዚህች ዓለም ሲመጡ አላህ ለባሪያዎቹ የመረጠውና የወደደውን የኢስላማዊ አቂዳ እምነት ይዘው ነው፡፡ ነገር ግን ሸይጧን ከእነ ሰራዊቱ ከዚህ የቀና የእምነት ጐዳና በማስወጣት በአስከፊ የባዕድ አምልኮና ሽርክ ውሰጥ እንዲዘፈቁ አድርጓቸዋል፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ﷺ) ይህንን በተመለከ በአስተላለፉት ሀዲስ፡-
«ማንኛውም ሰው የሚወለደው በኢስላም (በትክክለኛው እምነት) ላይ ነው፤ ከዚያ በኃላ ወላጆቹ አይሁድ ወይም ነሳራ ወይም እሳት አምላኪ ያደርጉታል፡፡»” ብለዋል
የሀዲሱ አስላላፊ አቡ ሁረይራ በዚህ ዘገባ መጨረሻ ላይ፡- ከፈለጎችሁ የሚከተለውን የቁርአን አንቀፅ አንብቡ፡-…
فِطْرَتَ اللَّهِ الَّتِي فَطَرَ النَّاسَ عَلَيْهَا ۚ لَا تَبْدِيلَ لِخَلْقِ اللَّهِ ۚ ذَٰلِكَ الدِّينُ الْقَيِّمُ وَلَٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ [٣٠:٣٠]
«የአላህን ፍጥረት ያቺን አላህ ሰዎችን በአርስዎ ላይ የፈጠረባትን (ሃይማኖት ያዙዋት) የአላህን ፍጥረት እና (ሃይማኖት) መለወጥ የለም፣ ይህ ቀጥተኛ ሃይማኖት ነው፤ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች አያውቁም፡፡»”
(አል ሩም 3ዐ) (ቡኻሪ እንደዘገቡት)
ከአባታችን አደም ዘመን አንስቶ እስከ ነብዩላሂ ኑህ ዘመን ድረስ የነበሩት ሕዝቦች በዚህ የእምነት ጐዳና በቀጥተኛነት ይጓዙ እንደነበር በቁርአንና በሐዲስ ውስጥ በበርካታ አንቀጾች ተገልጿል፡፡ የተለያዩ ሰሃባዎች ንግግሮችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡
ከእነዚህ የቁርአን ማስረጃዎችም በአል-በቀራህ ቁጥር 213 ላይ አላህ እንዲህ ይላል፡-
كَانَ النَّاسُ أُمَّةً وَاحِدَةً فَبَعَثَ اللَّهُ النَّبِيِّينَ مُبَشِّرِينَ وَمُنذِرِينَ
البقرة: ٢١٣
‹‹((ሰዎቹ ሁሉ አንድ ሕዝብ ነበሩ፤ (ተለያዩ)፡፡ አላህም ነቢያትን አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች አድርጎ ላከ፡፡))›› (አል በቀራህ 213)
በዓቂዳ መለያየት እንዴት ተከሰተ?
ከሰሃባዎች ዘመን አንስቶ ያሉ የቁርአን ትንታኔ (ተፍሲር) ሊቃውንት በነብዩላህ አደም እና በኑህ አፈጣጠርና ትውልድ መካከል የአስር ክፍለ ዘመናት ልዩነቶች እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህ ክፍለ ዘመናት ውሰጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አላህ ሰዎችን በፈጠረበት፣ ለባሪያዎቹ በመረጠውና በወደደው በትክክለኛው የኢስላማዋ አቂዳ የእምነት መንገድ ይጓዙ እንደነበረም ይገልፃሉ፡፡
በክፍለ ዘመናቱ መጨረሻም ላይ ግን ሸይጧን ከክፍለ ሰራዊቱ ጋር ተባብሮ በከፈተው በልብ የሚስብ ዘመቻ የሰው ልጅ የአቂዳን የእምነት ፈለግ በመሳት እጅግ አስከፊ ወደሆነው የባዕድ አምልኰና የሽርክ አዘቅት ውስጥ መውደቅ ችሏል፡፡
ኢማሙል ቡኻሪ በቅዱስ ቁርአን ሱረቱ-ነህ ውስጥ ስለተጠቀሱት የወድ፣ሱዋዕ፣የጉስ፣ የዑቅ እና ነስር የተባሉት ሰዎች ከአብድላህ ኢብኑ አባስ ንግግሮች የሚከተለውን ዘግበዋል፡፡
“…እነዚህ ከኑህ መላክ በፊት የነበሩ ደጎግ የአላህ ባሪያዎች ሰዎች ስሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ደጋግ ባሪያዎች በሞቱ ጊዜ ሕዝቡ ክፉኛ ማዘኑን በመመልከት ሸይጧን ወደ ሕዝቡ በመምጣት እነዚህን ደጋግ የአላህ ባሪያዎች ለማስታወስ ይረዳችሁ ዘንድ በየመቀመጫ ስፍራቸው (የመታሰቢያ) ምስላቸውንና ሀውልታቸውን አኑሩ፣ በየስማቸውም ሰይሟቸው በማለት መልዕክት አስተላለፈ፡፡ ሰዎቹም የተባሉትን ተገበሩ ነገር ግን በዚያን ወቅት እነዚህ ምስሎች አልተመለኩም ነበር፡፡ ይህኛው ትውልድ አልፎ ትውልድ በትውልድ በተተካ ጊዜ (አላህን በብቸኛነት የማምለክ የተውሂድ) እውቀት በተረሳ ጊዜ እነዚያ ምስሎች ተመለኩ፡፡” ይላል ዘገባቸው
በዚህም ምክንያት የሰው ልጆች ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱ ነብያትን በተከታታይ ላከ መሰረታዊ መልዕክታቸውንም ይህንኑ ጥመት ማሳወቅ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment