መቼም የሰው ልጅ ራሱን ከክስረት ለማዳን ሁሌም ይጥራል ይባዝናል። ይህንን የማያደርግ አንድም የትክክለኛ አእምሮ ባለቤት የለም ። ዳሩ ግን ከክስረት ለመዳን የሚጥርበት ሁኔታ አሊያም ድኛለው ብሎ የሚያምንበት ነፃነት እንደ ሰውዬው አስተሳሰብ እና ግንዛቤ የተለያየ ነው ። አንዱ ክስረት አድርጎ ሚመለከተው ድህነትን ሲሆን ፡ በሀብት ጮቤ የረገጠ እለት ነፃ መውጣቱን ያውጃል ። ሌላው ስልጣን ማጣትን ክስረት አድርጎ ሲመለከተው ፡ በምንም መልኩ ይሁን የወንበርን ኮርቻ የተቆናጠጠ እለት ክስረትን ድል እንደነሳ ያፀድቃል ። ሌላው ህመምን ከነገር አለሙ ያሰናበተው ክስረት አድርጎ ሲያየው በጤና ዘውድ እንዳሻው የቧረቀ እለት ነፃ ነቱን ያረጋግጣል ። መቼም ለናሙና ያህል ይህ ተጠቀሰ እንጂ ሌላም ብዙ ነገሮችን በዚህ መልኩ መውሰድ ይቻላል ። ነገር ግን ወደ ዋናው አላማዬ ልምጣና አላህ ሱ ወ የሰው ልጆች ምንም ገንዘባቸው ቢበዛ ፡ አጃቢያቸው ቢበረክት ፡ የስልጣናቸው ደውል ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ቢያስተጋባ ፡ ፍፁም ክስረት ውስጥ እንደሆኑ ተናግሯል ። ታዲያ ከዚህ ክስረት ነፃ በመውጣት የሚድኑትንም በሚገባ ጠቅሷቸዋል ። የነዚህም ሰዎች በህሪ አራት ታላቅ አላማና ግብን ያነገቡ ናቸው።
“በጊዚያቱም እምላለው ። ሰው ሁሉ በእርግጥ ከሳራ ውስጥ ነው ። እነዚያ ያመኑትና፡ መልካሞችን የሰሩት ፡ በእውነትም አደራ የተባባሉት ፡በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ።” (103:1-3)
ይህን አንቀፅ ሸይኽ ሙሀመድ ቢን አብዱል ወሀብ አላህ ይዘንላቸውና እንዲህ ሲሉ አብራርተውታል። በሰው ልጆች ላይ ማወቅ ግዴታ የሚሆንባቸው አራት ነገሮች አሉ እነርሱም
1_ እውቀት ነው ።ይህም እውቀት ( አላህን ሱ ወ ነብዩንና ኢስላምን በማስረጃ ማወቅ) ነው።
2_ ይህን እውቀት በተግባር ማዋል ነው ።
3_ ወደዚህ ጥሪ ወይም ዳእዋ ማድረግ ነው ።
4_ በነዚህ ነገሮች ላይ መታገስ ነው ።
አላህን ባማሩት ስሞቹና ባህሪዎቹ እማፀነዋለው እኔንም እናንተንም ባጠቃላይ ሙስሊሞችን ከክስረት ከሚድኑት እንዲያደርገን አሚን !
No comments:
Post a Comment