ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ከ«ጀበለሩማት» ላይ ያስቀመጧቸው ቀስት አስወንጫፊዎች በጦርነቱ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። በኻሊድ ቢን ወሊድ የሚመራ ጦር በዚህ አቅጣጫ ሶስቴ ሰብሮ ለመግባትና ሙስሊሞችን ከጀርባቸው ለማጥቃት ቢሞክርም አልተሳካለትም። ጊዜው ኡሁድ ነበር፤ በድር በተጠናቀቀ በአመቱ። ቁጥረ አናሳው የሙስሊም ሰራዊት ድል እየቀናው ሄደ።
ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ለቀስት አስወንጫፊዎች ሶሃባዎች ልዩ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር «የጦርነቱ ሚዛን ምንም ይሁን ምን ቦታቸውን እንዳይለቁ» ይህ ጥብቅ ትዕዛዝ ቢሰጣቸውም ሙስሊሞች የጠላትን ገንዘብ ሲማርኩ ሲመለከቱ ዱኒያ አታለለቻቸው!!!! ጓጉ። «ምርኮ እንሰብስብ ወገኖቻችን አሸንፈዋል ከእንግዲህ ምን እንጠብቃለን» ተባባሉ። መሪያቸው አብደላህ ኢብን ጁበይርና ግን «የአላህ መልዕክተኛ ያሏችሁን እረሳችሁን?» አላቸው። ሆኖም ብዙሀኑ ለአብደላህ ድምፅ ጆሮ አልሰጡም። «ሄደን ምርኮ መሰብሰብ አለብን» አሉና አርባ የሚሆኑ ቀስተኞች ቦተቸውን ለቀው ወደ ምርኮው ገሰገሱ። የነቢዩን መመሪያ ጣሱ። ይህ ሲሆን የሙስሊሞች ጀርባ ተጋለጠ። አብደላህ ኢብን ጁበይርና ዘጠኝ ባልንጀሮቹ ብቻ በነቢዩ ቃል ፀኑ።
ኻሊድ ቢን ወሊድ(ከመስለሙ በፊት) ይህን ወርቃማ እድል ተጠቀመበት። በፍጥነት በጀርባ ዞሮ ቀሪዎቹን ቀስተኞች አስወገደ። ከዚያም ሙስሊሞችን ከኋላ አጠቃ። የቁረይሽ ፈረሰኞች የጦርነቱ ሁኔታ መለወጡን በጩኸት ለወገኖቼቸው አበሰሩ። በሙስሊሞች ላይም ተረባረቡባቸው። የጣኦታውያን ባንዲራ ተነሳ፤ በሱም ዙሪያ ተሰባስበው በፅናት ተዋጉ። ሙስሊሞችን ከፊትና ከኋላ በሁለት እሳት ገረፏቸው። ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ክፉኛ ቆሰሉ። ጡሩራቸው ጉንጫቸው ላይ ተሰካ፤ ጥርሳቸው ተሰበረ። ትከሻቸው ላይ ተመቱ። ራሳቸው ተፈነከተ። ደማቸው ፈሰሰ….
የዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያቱ የቀስተኞቹ ስህተት ነበር። የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ትዕዛዝ ችላ ብለውም ጣሱ፤ የዛን ቀን 70 ሶሀቦች ተገደሉ፤ ሙስሊሞች ተሸነፉ። ሙስሊሞች ሆይ ምንግዜም የአላህና የነቢዩን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቃል ልንጠብቅ ይገባናል!!! አሊያ ግን ቃሉን መጣስ ትርፉ ሽንፈት ነው። አላህ ይጠብቀን።
No comments:
Post a Comment