የወላጆች ሃቅ
ጌታዬ ሆይ እኔን በህፃንነቴ እንደተንከባከቡኝ እዘንላቸው!
“ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ። በወላጆቻችሁም መልካምን ስሩ። በአንተ ዘንድ
ሆነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ እፉ አትበላቸው። አትገልምጣቸውም። ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው ።
ለሁለቱም የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው። ጌታዬ ሆይ፡ በህፃንነቴ (በርህራሄ) እንዳሳደጉኝ እዘንላቸውም በል።”(ኢስራእ:23)
ኢብኑ መስዑድ ባወራውና ሃዲስ ላይ
የአላህ መልእክተኛ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብሎ መጠየቁን ተናግሯ ።
የአላህ መልእክተኛ ሆይ የትኛው ስራ ነው አላህ ዘንድ በላጩና ተወዳጁ? ነብዩም እንዲህ ሲሉ መለሱ “ሰላትንበወቅቱ
መስገድ” ከዚህስ ሌላ? አልኳቸው። “ወላጆችን መንከባከብ” አሉኝ። ከዚህስ ሌላ? አልኳቸው። “በአላህ መንገድ ላይ
መታገል(ጂሃድ) ነው” አሉኝ። (ቡኻሪና ሙስሊም)
ከላይ በጠቀስናቸው የቁርአን አንቀፅና ሃዲስ የወላጆችን ታላቅነት ሊሰጣቸው ሚገባውን መብትና እንክብካቤ ቁልጭ አድርጎ
አስቀምጧል። አዎ! መቼም ማንም ቢሆን ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያላቸውን ውለታ አይክድም። ይህም ውለታ ተቆጥሮ ባይዘለቅም
ከመሰረቱ ለመጀመር ያህል ፦
ወደዚህች ምድር ለመምጣቱ ሰበብ ናቸው። እንዴታ ዝንፍ እንኳ
ባላለ መልኩ እንግድነቱን ተቀባዮች። አይዞህ ባይ አስተናጋጆች አስለማጆች።
ከዚህ
በኋላም የእድገቱ ኡደት "ሀ" ብሎ ይጀምራል። እርሱ እንዲመቸው ተቸገሩ። እንዲጠግብ ተራቡ። እንዲጠጣ ተጠሙ።
እንዲለብስ ታረዙ። እንዲተኛ አነጉ። ባጭሩ በእነርሱ የደህንነት ሂሳብ እርሱን ለማሰንበት አስፈላጊ መስዋእትነትን ሁሉ ወደፊት
እንጂ ወደኋላ ሳይሉ ከፈሉ። ታዲያ ኢስላም ይህንን ውለታቸውን ተገቢውን ትርጓሜ ሰጥቶታል። አላህ (ሱብሃነሁ ወተዓላ) እርሱን
ከመገዛት ትእዛዝ በውሃላ ለወላጆች በጎና መልካም መዋልን አዟል። እንግዲህ እኛም ይህን ተገንዝበን ባፋጣኝ ወላጆቻችንን
ልንንከባከብና መብታቸውን ልንጠብቅ ግድ ይላል። በአላህና በመልእክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂወሰለም) ትእዛዝ እስካልመጡብን ድረስ
አቅማችን በፈቀደው ሁሉ ልንንከባከባቸው ይገባል። እነርሱን በማስደሰት የዱዓቸው ተሸላሚዎች መሆን አለብን። ካላፉ በኃላ
የቁጭትና የፀፀት አዝመራን አጫጅ እንዳንሆን ካሁኑ ቆም ብለን እናስብበት። ለወላጆቹ ተገቢውን መብት ያልሰጠ ወይም የበደለ
መልካም ነገር ለእርሱ የሰማይ ዳቦ ነው። እውቀት አይገራለትም። ተቅዋ አይሰክንለትም። ደስታ የውሃ ሽታ ይሆንበታል። ነገ ጠዋት
ወልዶ ሲከብድ ደግሞ የበደሉን ፅዋ በገዛ ልጆቹ ይጎነጫል። ስለዚህ ከአሁኑ ይቅርያቸውን ሊቸሩን ይገባል። የሞቱም ካሉ ኢስላም
ለእነርሱም መብት ከመስጠት አልቦዘነም።
1)
ዱዓ ማድረግ።
2)
የተለያዩ ምፅዋቶችን ወይም ሰደቃ መስጠት።
3)
ንዛዜያቸውን መፈፀም
4)
እዳ ካለባቸው በፍጥነት መመለስ።
5)
ወዳጆቻቸውን መጠየቅ ናቸው።
ለመተዋወስ
ያህል ነው። አበቃሁ። አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የወላጆቻችንን እድሜ በእርሱ አምልኮ(ጣዓ) ያርዝምልን። እኛንም ለእንክብካቤያቸው
ያድለን። የሞቱትንም በጀነትላይ ያሰባስበን። አሚን
No comments:
Post a Comment